ባሕር ዳር፣ ግንቦት 30/2017 ዓ/ም (ባ/ዉ/ፍ/አገ/ድ/)
የባሕር ዳር ዉኃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ከ2014 እስከ 2017 በጀት ዓመት ድረስ ያለዉ የንፁህ መጠጥ ዉኃ አቅርቦትና ሃብት አስተዳደር ዉጤታማነትን በተመለከተ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የክዋኔ ኦዲት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የክዋኔ ኦዲቱን ጭብጥ፣ የኦዲት የመገምገሚያ መስፈርቶችንና የኦዲቱን ዘዴዎች በተመለከተ የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የክዋኔ ኦዲት ማኔጀርና ኦዲተሮች ከአገልግሎት ድርጅቱ የማኔጅመንት አባላት ጋር ግንቦት ግንቦት 30/2017 ዓ/ም ዉይይት አካሂደዋል፡፡
የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የክዋኔ ኦዲት ማኔጀር የሆኑት አቶ ወንድሙ ገብሬ በዉይይቱ ወቅት የክዋኔ ኦዲት ማለት የመንግስት መስሪያ ቤቶች የኢኮኖሚ፣ የብቃትና የዉጤታማነት ኦዲት ሲሆን የመንግስት በጀት በተጨባጭ ስራ ላይ ስለመዋሉ የሚያረጋግጥ የኦዲት ዓይነት ነዉ ብለዋል፡፡ በተያዘዉ በጀት ዓመትም የአገልግሎት ድርጅቱ ከ2014 እስከ 2017 በጀት ዓመት ድረስ ያከናወናቸዉን የንፁህ መጠጥ ዉኃ አቅርቦትና ሃብት አስተዳደር ዉጤታማነትን ኦዲት የሚደርግ የኦዲተሮች ቡድን እየሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የባሕር ዳር ዉኃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ይርጋ አለሙ በድርጅቱ ካሁን በፊት የክዋኔ ኦዲት ያልተደረገ መሆኑን አንስተዉ በያዝነዉ በጀት ዓመት ኦዲት መካሄዱ የአገልግሎት ድርጅቱን በጀት በቁጠባና በብቅት በመጠቀም ዉጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ያስችለናል ብለዋል፡፡ የድርጅቱ የክዋኔ ኦዲት በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊዉን እገዛ እንደሚያደርጉ ጨምረዉ ገልፀዋል፡፡
የክዋኔ ኦዲቱ የዕቅድ ዝግጅት፣ የዋና ግኝቶች ዝርዝር ትንተና፣ የሪፖርትና ማጠቃለያ እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ፕሮግራሞችን የያዘ ሲሆን የዕቅድ ዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዉ የዋና ዋና ግኝቶች ዝርዝር ትንተና ስራ እንደተጀመረ ከኦዲተሮች ቡድን ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል፡፡




