ባሕር ዳር፣ ግንቦት 28/2017 ዓ/ም (ባ/ዉ/ፍ/አገ/ድ/) በባሕር ዳር ዉኃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት በ2017 በጀት ዓመት ሊሰሩ የታቀዱ የፕሮጀክት ስራዎች ያሉበት ደረጃ ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከመጡ የፕሮጀክት ስራዎች ገምጋሚ ቡድን ጋር ግንቦት 27/2017 ዓ/ም ሰፊ ግምገማና የመስክ ምልከታ ተካሂዷል፡፡
የአገልግሎት ድርጅቱን የአዲስ ጉድጓድ ቁፋሮ ስራ፣ የዉኃ ግፊት፣ የማሰራጫና የማስፋፊያ መስመሮች እንዲሁም የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም የፕሮጀክት ስራዎች አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የድርጅቱ ምክትል ስራ አስኪያጅና የመጠጥ ዉኃ አቅርቦትና ተቋማት አስተዳደር የስራ ሂደት መሪ አቶ ድረስ አስማረ ሲሆኑ በቀረበዉ ሪፖርት ዙሪያ የገምጋሚ ቡድን አባላት ከድርጅቱ አመራሮች ጋር ሰፊ ግምገማዊ ዉይይት ተካሂዶበታል፡፡ ለዕቅዱ ስኬታማነት ከፍተኛዉን አስተዎፅኦ ያበረከተዉ ስራዎችን በራስ አቅም ለመፈፀም ጥረት መደረጉና ይህ ደግሞ የፕሮጀክት ወጪዉንም በእጅጉ እንደቀነሰላቸዉ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ይርጋ አለሙ አብራርተዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የኢኮኖሚ ዘርፍ አማካሪና የከተማ አስተዳደሩ የፕሮጀክት ስራዎች ገምጋሚ ቡድን አባል አቶ አስፋዉ ገበየሁ የአገልግሎት ድርጅቱ በሪፖርት ያቀረበዉ እና በመስክ ምልከታ ያረጋገጥነዉ ድርጅቱ የተሻለ የፕሮጀክት ስራ አፈፃፀም ያለዉ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ይህ ዉጤት የመጣበት ምክንያትም የድርጅቱ የስራ መሪዎች ለፕሮጀክት ስራዎች የተለየ ትኩረት መስጠታቸዉና የራሳቸዉን አቅም አሟጠዉ መጠቀማቸዉ ነዉም ብለዋል፡፡ ይህ አፈፃፀማቸው ለሌሎች በከተማ አስተዳደሩ ለተጀመሩ የፕሮጀክት ስራዎች በሞዴልነትና በአስተማሪነት የሚወሰድ እንደሆነም ጨምረዉ አብራርተዋል፡፡




