ባህርዳር፤ መጋቢት 15 / 2017 የባህ/ዉ/ፍ/አገ/ድርጅት
የባህር ዳር ዉኃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ሰሞኑን የአለም ዉኃ ቀንን ከደንበኞች ፎረምና ከአጋር አካላት ጋር በአከበረበት ወቅት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ይርጋ አለሙ እንደገለፁት እያደገ የመጣዉን የከተማዉን የህዝብ ቁጥር ታሳቢ ያደረገ የዉኃ አቅርቦት ስራ ከወዲሁ ታቅዶ በፕሮጀክት ሊሰራ ይገባል፡፡
ዉኃ አገልግሎቱ አሁን ላይ የዉኃ ችግር እንዳይባባስና የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳይሆን በራሱ አቅም ከፍተኛ ወጭ በማዉጣት በያዝነዉ በጀት አመት ብቻ አራት ጉድጓዶችን አስቆፍሮ ወደስራ በማስገባት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዉ ነገር ግን ይህ ጊዜያዊ መፍትሄ እንጅ በከተማዋ ያለዉን የፈረቃ ፕሮግራም ሙሉ በሙሉ ሊያስቀር የሚችል አይደለም ብለዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የተጠቃሚ ፍላጎትና የአቅርቦት ችግር ነዉ ያለዉ፤ ለዚህም ተጨማሪ ዉኃ ማምረት አለብን ይህን ለማድረግ ደግሞ እኛ ብቻ ሰርተን የህዝቡን ጥያቄ አናረካም በመሆኑም የፌደራልና የክልል መንግስታት እንዲሁም ከተማ አስተዳደሩ የድርጅቱን ስራ ሊደግፉ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ዉኃ አገልግሎቱ ተጨማሪ ዉኃ ከማምረትና ከጥገና ስራ በተጨማሪ ዘላቂ የመጠጥ ዉኃ አቅርቦት ስራ ለመስራት በፕሮጀክት የሚሰሩ የዲዛይንና ሌሎች የጥናት ስራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዉ ጥናቱ እንደተጠናቀቀ ለሚመለከታቸዉ የሥራ ኃላፊዎች በማቅረብ ገንዘቡን በብድርና በእርዳታ በማሰባሰብ ወደ ግንባታ ስራ እንደሚገባና ለስራዉ የሁሉም አካል ርብርብ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
የዉኃ አገልግሎቱ ምክትል ስራ አስኪያጅና የገ/ግ/ፋ/ንብ/አስ/ የስራ ሂደት መሪ አቶ በሪሁን አለሙ በበኩላቸዉ ድርጅቱ ያለዉን በጀት በሙሉ አሟጦ ዉኃ አቅርቦት ስራ ላይ እያዋለ እንደሚገኝ ጠቅሰዉ ደንበኛዉ በሚጠይቀዉ ልክ ለመስራት ግን ፋይናንስ ትልቅ ማነቆ እንደሆነባቸዉ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የደንበኞች ፎረም አባላት ደንበኞች ያሉባቸዉን ዉዝፍ የዉኃ ሂሳብ እንዲከፍሉ በማድረግ አስተዋፆአችሁ ከፍተኛ በመሆኑ ለደንበኞቻችን ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በመስራት ልታግዙን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በክልሉ ካሉ ከተሞች በዝቅተኛ ታሪፍ ዉኃ እያቀረበ ያለዉ የባህር ዳር ዉኃ ፍሳሽ አገልግሎት ነዉ ያሉት አቶ በሪሁን ድርጅቱ በወር ሌሎች የጥገናና የኦፕሬሽን ሰራዎችን ሳይጨምር ለመብራት ብቻ እስከ አምስት ሚሊየን ብር እየከፈለ እንደሚገኝና ይህ ችግር ወደፊትም የድርጅቱ ትልቅ ፈተና ሁኖ እንደሚቀጥል ስጋታቸዉን አመላክተዋል፡፡
የዉኃ አግልግሎቱን የአምስት አመት የእድገት ጉዞና ፈተናዎችን ያቀረቡት የድርጅቱ የህዝ/ ግን/የደን/ አገ/ የስራ ሂደት መሪ አቶ ደስታ አንለይ ደግሞ በ2017 በጀት አመት አጋማሽ ከ150 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን በሰነድ አቅርበዉ ከ69 ሚሊየን ብር በላይ ለመደበኛና ከ79 ሚሊየን ብር በላይ ደግሞ ለካፒታል ስራዎች ወጭ መደረጉንና የደንበኞች ቁጥርም 66 ሽህ መጠጋቱን ዘርዝረዋል፡፡
የደንበኞች ፎረም ሰብሳቢ አቶ ክንዴ ይታየዉ ደግሞ ፎረሙ በደንበኞችና በዉኃ አገልግሎቱ መካከል እንደ ድልድይ ሁኖ በማገልገል ችግሮችን እየፈታ እንደሚገኝ ጠቅሰዉ ድርጅቱ ቆጣሪ ንባብ ላይ ያለዉ አስራር ደካማ በመሆኑና ከከተማዉ ስፋትና ከደንበኞች ብዛት አንፃር ያሉት ቆጣሪ አንባቢዎች አነስተኛ በመሆናቸዉ ለዚህ ተመጣጣኝ የሆነ ቆጣሪ አንባቢ መመደብና አንባቢዎቹ ሙሉ ጊዜያቸዉን ስራዉ ላይ እንዲያጠፉ መደረግ አንዳለበት አሳስበዋል፡፡