የባሕር ዳር ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ከቪተንስ ኢቪደንስ ኢንተርናሽናል (Dutch Water Operators) ጋር በመተባበር የንጹህ የመጠጥ ውኃ የሚያገኝባቸውን የውኃ ምንጮች የተፋሰስ ልማትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የውኃ አገልግሎት ለማስፈን ከሚመለከታቸው ሃያ ሁለት ባለድርሻ እና አጋር ድርጅቶች ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ከጥቅምት 27 እስከ ጥቅምት 30/2018 ዓ.ም የቆየ የግንዛቤ ፈጠራ ውይይት በአዲስ አበባ ከተማ አድርጓል፡፡ የውይይቱ ዓላማ ውኃ አገልግሎቱ በዋናነት ለባህር ዳር ከተማ ህዝብ ውኃ የሚያቀርብባቸውን በኢንፍራንዝ ተፋሰስ ስር የሚገኙትን ሶስት ምንጮች ማለትም አረቄ ምንጭ፣ ሎሚ ምንጭ እና ጥቁር ውኃ ምንጭን (በአሁኑ ወቅት በሰከንድ 400 ሊትር ንጹህ ውሃ ለባህር ዳር ከተማ ያቀርባሉ) ተፋሰሳቸውን በመጠበቅና በአየር ንብረት ለውጥ ሳይበገሩ በቂ እና ያልተበከለ ውኃ በዘላቂነት እንዲያቀርቡ ለማድረግ የሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ተቀናጅተው ምን መስራት እንዳለባቸው ግንዛቤ የመፍጠርና በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ማስቻል ነው፡፡ ተፋስሱን የሚመለከት ጥናቶች በዶ/ር አትክልት ግርማ እና በጥናት ቡድኑ አካል በሆኑ ባለሙያዎች የቀረቡ ሲሆን የምንጮችን ተፋሰስ በመንከባከብ እና በተፋሰሱ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎችን የባለቤትነት ስሜት ይዘው እንዲሰሩና እንዲሁም እንዴት የልማቱ ተጠቃሚ እናደርጋቸዋለን የሚሉና የሌሎች አካባቢ መልካም ተሞክሮዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የውኃ አገልግሎቱም አስተማማኝና ጥራቱን የጠበቀ ውኃ ለማህበረሰቡ ለማቅረብ እና እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጡ አዳጋዎችን ተቋቁሞ ውኃ ማቅረብ እንዲችል ከምንጮች ተፋሰስ ጀምሮ በዘላቂነት አስቦ መስራት እንዳለበት በጥናቱ ተመላክቷል፡፡ የባሕር ዳር ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይርጋ ዓለሙ ድርጅቱ እስከዛሬ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ የነበረው መደበኛና አስቸኳይ ሥራዎችን መሆኑን ጠቅሰው ድርጅቱ በ2017 ባስጠናው ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ በተገለጸው መሰረት የውኃ ምንጮች በዘላቂነት ጥራቱን የጠበቀና አስተማማኝ ውኃ እንዲሰጡ ለማድረግ የሚሰሩ ሥራዎችን ባለቤት ሆኖ ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት እንዲሁም በተፋሰሱ ከሚገኙ ማህበረሰቦች ጋር በመተባበር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የውኃ አገልግሎት እንዲኖር ለማድረግ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡ በውይይቱም ማጠቃለያ ላይ ሥራውን በዋና አስተባባሪነት የሚያንቀሳቅሱ ሰባት የሚመለከታቸው ተቋማትን በኮሚቴነት በመምረጥና የሥራ ድርሻ በመከፋፈል ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
